የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአስተዳደርና ልማት ተ/ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር አታክልት ረዳ አዲሱን ፕሬዝዳንት በማስተዋወቅ መድረኩን ከፍተዋል፡፡ የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ብርሃነ መስቀል ጠና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፔዳጎጂ፣ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በትምህርት እቅድ እና አስተዳደር፣እንዲሁም ፒ.ኤ.ቺ.ዲያቸውን በትምህርት አመራር በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ስራ አመራር ላይ መስራታቸውን ገልፀዋል፡፡

ከልምድ አንፃር፣የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር፣ርዕሰ-መምህር፣ የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዲን፣ ከዛም የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አማካሪ፣ከህዳር 2008ዓ.ም. ጀምሮ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ሆነው እሰከተሾሙበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ስራ እመራር ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ሆነው እንደሰሩ ተናገረዋል፡፡ፕሬዝዳንቱ ራሳቸውን ለማሕበረሰቡ ካስተዋወቁ በኋላ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን ወደ ሙሉ ዩኒቨርሲቲነት ለማሸጋገር ምንም ነገር ሳይከፋፍለን በጋራ ሆነን ሁላችንም በተሰማራንበት ሙያ ጠንክረን መስራት አለብን ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ይህ ተቋም ምርጥ የከተማ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ይፈልጋል፤ እኛም ራሳችንን አውቀን ድርሻችንን ለይተን ችግሮቻችንን በውይይት ፈተን ተቋማችንን አሁን ካለበት ብሔራዊ ደረጃ ወደ አለም አቀፋዊ ደረጃ ማድረስ ይጠበቅብናል፤የትምህርት ልማት ሠራዊት ገንብተን፣እያንዳንዷን ቀን የትምህርት ቀን በማድረግ የማስተማሪያ ብቻ ሳይሆን የመማማሪያ ቀን ማድረግ እንችላለን፡፡በትውውቁ መጨረሻ ላይ ፕሬዝዳንቱ ሊያተኩሩ የሚገባቸው ነገሮች ላይ እና ምን ዓይነት መሪ መሆን እንደሚገባቸው ከተሳታፊዎች በተሰጠ እስተያየት ላይ ምላሽ ሰጥተዋል ::በመጨረሻም ዶ/ር ብርሃነ መስቀል ጠና ትምህርት ሚኒስቴር በሚሰሩበት ወቅት ለተቋማችን ያደረጉትን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ዶ/ር አታክልት ረዳ  በዝርዝር አብራርተዋል፤ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ አሳውቀዋል፡፡

 

                           የዘገበው የህዝብና ውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ነው፡፡